የኢትዮጵያ ብሎጎች ምን ጻፉ ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 6

አለማየሁ ገላጋይ እና በውቀቱ ስዮም በሳምንታዊው የፍትህ ጋዜጣ ላይ ስለኢትዮጵያና ጃፓን፣ ስለአጼ ቴዎድሮስና ስለአንድ የጃፓን ንጉሥ ክርክር ማካሄድ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል:: እኔም ሳምንት በመጣ ቁጥር የነዚህን ጸሀፍት ክርክር ለማንበብ መናፈቅ ጀምሪያለሁ:: ምንም እንኳ በውቀቱ በዚህ ሳምንት ክርክሬን አብቅቻለሁ ቢልም ሳምንትአለማየሁ ምን ሊመልስ እንደሚችል ለማወቅ ግን መጓጓቴ አልቀረም:: ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ግን እንዲህ ያሉትን ያደባባይ ክርክሮች በተመለከት “በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ለምንጽፍ ሁሉ እየተናገሩ አለማነጋገር፣ እያሰቡ አለማሳሰብ” በሚል ርእስ አንድ ጽሁፍ አስነብበዋል:: ይህቺ ጽሁፋቸው በብሎጋቸው ታትማ ስለነበር የዚህ ሳምንት የብሎግ ክለሳዬ ፊትአውራሪ አድርጊያታለሁ:: አንድ አንቀጽ ላቃምስና ወደ ሌሎች ብሎጎች ልለፍ::

“ሀሳብን በጋዜጣ ማውጣት አደባባይ መውጣት ነው፤ አደባባይ የሚወጡበት ጉዳይ የግል ሳይሆን የአገርና የሕዝብ ነው፤ መሆን አለበት፤ አደባባይ በወጣው ጉዳይ ላይ በአገርና በህዝብ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ባለቤት ሊሆንበት ይችላል፤ በባለቤትነት ሊተችበት ይችላል፤ በጉዳዩ ላይ የሞቀ ክርክር ቢደረግበት ሁላችንም በብዙ መንገድ ተጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለን፤ ነገር ግን እስከዛሬ የሚታየው አዲሱ ልምድ ከላይ ባለስልጣኖች እንደልባቸው ይናገራሉ፤ በግድም ይሁን በውድ አብዛኛው ሰው ይሰማቸዋል፤ ባለሥልጣኖቹን በማስተጋባት ቴሌቪዥኑና ራዲዮው ደጋግመው እስቲሰለች ድረስ ያሰማሉ፤ በግድም ይሁን በውድ የባለሥልጣኖቹ ንግግር ለብዙ ሰዎች ጆሮ ይደርሳል፤ ግን ጆሮ የደረሰ ሁሉ ወደልብ መተላለፉን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፤ በአንጻሩ በግል ጋዜጦች ላይ የሚወጡት የተለዩና የተለያዩ ሀሳቦች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አመራሩን የሚተቹ ናቸው፤ እነዚህን ጋዜጦች የሚያነብቡ በጣም ጥቂቶች ናቸው፣ ጋዜጦቹን የሚያገኙዋቸው በገንዘባቸው እየገዙ በመሆኑ የሰዎችን ቀልብ መሳባቸው ይታወቃል፤ እነዚህን ትችቶች ባለሥልጣኖቹ ጉዳያቸው አድርገው የሚያነቡዋቸው አይመስለኝም፤ የእነሱ ንቀት ሚስትህ አረገዘች ወይ ቢሉት፣ ማንን ወንድ ብላ! እንዳለው ነው መሰለኝ፤ ባለሥልጣኖቹ ሁለት ጥቅሞችን ያጣሉ፤ አንደኛ የተቺዎቹን ሀሳብ መረዳትና ከራሳቸው ሀሳብ ጋር የማመዛዘን ዕድሉ ያመልጣቸዋል፤ ሁለተኛው ሕዝቡ በነፃነትና ያለምንም ግዴታ ትችቱን በማንበቡ ብቻ የሚያስተላልፈውን መልእክት ሳያውቁት ይቀራሉ፤ የዚህ ውጤት የአገር ጉዳት ነው፤ እንግዲህ እነሱ የሚናገሩትን ይናገራሉ፤ ሌላውም የሚናገረውን ይናገራል፤ በሁለቱም ወገን የሚነገረው ስለአንድ አገርና ስለአንድ ሕዝብ ነው፤ በሁለቱም በኩል የተያዘው ፈሊጥ ሳያነጋገሩ መናገር ነው፤ ክፉ ሕመም ነው።”

ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ጠቅ ማድረግ በቂ ነው:: አልያም ያለፈውን ሳምንት ፍትህ ጋዜጣ ማንበብ::

ቀጠልኩ ሰሞኑን ሀገራችን የአለም ኢኮኖሚ ፎረምን አስተናግዳ ነበር:: ፎረሙ ብዙ ገጽታ ነበረው። ኢትዮጵያ እያሳየች ባለው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት የተነሳ የዚህ ፎረም አዘጋጅ እንድትሆን ተመርጣለች በመባሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስሜታቸውን ገልጽዋል:: የተደሰቱ ያልተዋጠላቸው እና ምንም ያልመሰላቸው ወይም ያልሞቃቸውም ያልበረዳቸውም ይገኙበታል:: ነገር ግን አቤ ቶክቻው ለማተኮር የፈለገበት ነጥብ በፎረሙ የሀገራት መሪዎች ውይይት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የተናገሩት ላይ ነው:: አቤ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ሽሙጣዊ ሰላምታ ባቀረበበት ብሎጉ ውይይቱ ላይ የነበረውን ድባብ በሚከተለው መልኩ አቅርቧል:: አንድ አንቀጽ እንካችሁ::

ማንም ያልደፈርዎትን ሰውዬ ትላንት በአለም ኢኮኖሚ ፎረም መድረክ ላይ፤ “ዲሞክራሲን ከሚያፍኑ እንደ ቻይናን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር በይበልጥ የመተባበራችሁ ምስጢር ምንድነው?” ብሎ ሲያበቃ “አቶ መለስ ዙሪያ ጥምጥም ሳይሄዱ በቀጥታ ይመልሱልኝ” ማለቱን ስሰማ እንዴት ቢደፍራቸው ነው? ብዬ የደነገጥኩትን መደንገጥ የተበሳጨሁት መበሳጨት አይጠይቁኝ። ለነገሩ ግን እርስዎም እኮ ራስዎን አለቅጥ ለተቺ አጋለጡ። ትዝ ይልዎት እንደሆነ፤ በፎረሙ ላይ አወያይ የነበረችው ሴት አንድ ጥያቄ ጠይቃዎ ያልተጠየቁትን ሲያወሩ፣ ሲያወሩ፣ ሲያወሩ ቆይተው ሰዓቱን ከፈጁት በኋላ፤ “ጥያቄሽን ረሳሁት ምን ነበር ያልሽኝ?” ብለው ድጋሚ ሲጠይቁ ተሰባሳቢው በሙሉ እንዴት እንደሳቀብዎ እኔም እንዴት እንደተሸማቀኩልዎ ቢያዩኝ ለአንዱ ቀበሌ ሊቀመንበር ያደርጉን ነበር።

ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ጠቅ ያድርጉ:: ከዚህ ጋር በተያያዘ የጠቅላይ ሚንስትሩ በውይይቱ ወቅት የሰነዘሯቸው አስተያየቶች በሌሎች አለም አቀፍ ብሎጎች ላይም ወጥተው ነበር::በተለይ አፍሪካ ውስጥ ስለተንሰራፋው ሙስና ተጠያቂው ምእራባዊያን ኢንቪስተሮች ናቸው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ፈጣን ብቻ ሳይሆኖ ፍትሀዊ ነው ለኢኮኖሚ እድገት ዲሞክራሲ ወሳኝ አይደለም የሚሉት አስተያየተያየቶቻቸው ሰፋ ያለ ትኩረት አግኝተው ነበር:: የጠቅላይ ሚንስትሩን አስተያየቶች እና ውይይቱን በከፊል እዚህ ትይይዝ ላይ ጠቅ በማድረግ ማግኝት ይችላሉ::

ጠቅላይ ሚንስትሩ እነኝዚህን አስተያየቶች ይስጡ እንጂ ብሎገሮች/ጦማሪያን በሳቸው አስተያየቶች አይስማሙም እንዳውም ዲ ብራሀን የተሰኝ በእንግሊዝኛ የሚታተም ብሎግ የጠቅላይ ሚንስትሩን አስተያየት የሚያፋልስ ሰፋ ያለ ጥናታዊ መልክ ያለው ትንታኔ አትሟል:: ከክርክሩ ባሻገር የዲሞክራሲን እና የኢኮኖሚ እድገትን ግንኙነት ግንዛቢዮዎትን ለማዳበር የሚረዳ ጽሁፍ ነው:: እዚህ ላይ ጠቅ በማድረግ ጽሁፉን ያንብቡት:: ኢኮኖሚው አደገ ተመነደገ የሀብት ክፍፍልም ፍትሀዊ ሆነ ኢትዮጵያም የማር እና የወተት ምድር ሆነች ለሚሉ ወገኖች ስኳር እንኳ ማግኝት እንዴት እንደቸገረው ስኳር እንደገና በሚለው ጽሁፍ ተስፋዪ አለማየሁ አትቷል። ጽሁፉን እዚህ ላይ ጠቅ በማድረግ ያንብቡት።

ስለ ሰዎች ስንሰማ እንዴት መስማት እንዳለብን ሦስቱ ማጣርያዎች በሚል ርእስ ስለ ሃሜት ክፋት ያስነበበን ዳንኤል ክብረት ነው:: ጽሁፉን እዚህ ላይ ጠቅ በማድረግ ያንብቡት። ባለፈው ሳምንት ስለ አብዮት ያስነበበን በፍቄ በዚህ ሳምንት ደግሞ የጋንዲ፣ ኪንግ እና ማንዴላ መንፈስ በሚል ርእስ እኛ ኢትዮጵያውያኖች ከነእዚህ የዓለም ሃብቶች አንፃር ራሳችንን አይተነው እናውቅ ይሆን? ብሎ እራሳችንን እንድንጠይቅ የሚገፋፋ ጽሁፍ አሥነብቧል:: ጽሁፉን ትይይዙን ጠቅ በማድረግ ያንብቡት።

ወደው እና መርጠው ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ የውጪ ሀገር ዜጎች እና ስራዎቻቸው ያስነበበን ደግሞ ዘላለም ማልኮም ክብረት ነው:: ምንም እንኳ ዘላለም የእንግሊዝኛ ጦማሪ ቢሆንም ያነሰው ርእሰ ጉዳይ ከኢትዮጵያውያ ጋር የጠበቀ ግንኙንት ስላላቸው የውጪ ሀገር ዜጎች ስለሆነ በዚህ የአማርኛ ጦማር ክለሳ ውስጥ ላካትተው ግድ ብሎኛል:: ዘላለም የውጪ ሀገር ዜጎች ስለ ኢትዮጵያ ምን ያስባሉ የሚለውን ለመረዳት አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን አስር ፊት አውራሪ ምሁራን አቅርቧል:: ከነዚህም መሀከል ጀምስ ብሩስ ክርስቶፎር ክላፍም ዶናልድ ሊቭይን ክላውድ ሰምነር ይገኙበታል:: ሁሉንም ዝርዝር ለማግኝት ትይይዙን ጠቅ በማድረግ ያንብቡት።

ባለፈው ሳምንት አንድ የስነጽሁፍ ብሎግ አስተዋውቄ ነበር:: : ቤዋዬን:: ይህ ብሎግ በዚህ ሳምንት ደግሞ እውነት ቀመስ ልቦለድ አስነብቧል::ታሪኩ ስለስደት ነው:: አሳዛኝ ግን የበርካታ ኢትዮጵያውያን የህይወት እውነታ ታሪኩን ትይይዙን ጠቅ በማድረግ ያንብቡት።

አትሌቲክስ ለምትወዱ የፍሰሀ ተገኝ ብሎግ አመታዊው የዳይመንድ ሊግ አትሌቲክስ ውድድር ኳታር ዋና ከተማ ዶሀ ውስጥ ሲከፈት የተለያዩ አስደናቂና ያልተጠበቁ ውጤቶች ተመዝግበውበታል ይለናል:: ሀተታውን ለማንበብ እዚህ ጋር ጠቅ ያድርጉ:: መልካም ሳምንት::

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.