በዚህ ሳምንት የሀገር ቤት የህትምት ውጤቶችም ቢሆኑ የማህበራዊ ደረ፡ገጾች እና ብሎጎች በስፋት ሲያንሱ ሲጥሉ የነበሩት ቴዲ አፍሮን እና እጮኛው አመለሰትን ነበር:፡ ቴዲ አዲስ አልበም ስላወጣ እና የእጮኛውን ማንነት በራዲዮ ቃለ ምልልስ ወቅት ይፋ ስላደረገ ያገኝው ሽፋን ይመስለኛል:: ለነገሩ አቤ ቶክቻው ይህንን በማስመልከት የቴዲ ሰሞን ገባ ብሎ አልበሙን በማስመልከት ባለፈው ሳምንት አልበሙን በማድነቅ በተለይ የአልበሙ መጠሪያ የሆነውን ጥቁር ሰው የሚለውን ዘፈን ምንሊክን ዳግም ያነገሰ ብሎ ከትቦ ነበር:: አልበሙ ከመውጣቱ በፊትም ማርቆስ በእንግሊዝኛ የቴዲን አልበም ልገዛ የምገደድባቸው አምስት ምክኒያቶች ብሎ ጽፎ ነበር :: ዘላለም ማልኮም ክብረትም ጥቁር ሰው የሚለው ዘፈን የኢትዮጵያን ታሪክ ባጭሩ የሚያስተምር ነው ይለዋል:: ነገር ግን በፍቃዱ ዘሃይሉ የቴዲን አልበም የጠበቀውን ያህል ጥሩ አለመሆኑን ገልጾ አልበሙን ያልገዛባቸውን አምስት ምክኒያቶች ዘርዝሮ ጽፏል:: ዲ ብራሀን ደግሞ ተነባቢነት ያገኝ ሰፊ ዘገባ ይዞ ወጥቷል:: ሁሉንም አንብቧቸው የሰሞኑን ወሬ ጭብጥ በሚገባ ያስቃኞታል: ግንዛቤዎ ሙሉ እንዲሆን: ታዲያ የፎርቹንን እና የአድማስን የፊት ገጽ ዘገባ እንዳይረሱ:: የፎርቹን ድረ ገጽ ምናልባት ባይከፍትሎት ሸገር ትሪቡን ላይ ያገኙታል::
ቴዲ እና አልበሙ አነጋጋሪ ቢሆኑም ሌሎችም አበይት ጉዳዮች ነበሩ ምንም እንኳ የማህበራዊ ደረ፡ገጽ ተጠቃሚዎች እና ብሎጎች ለቴዲ የሰጡትን ትኩረት ባይሰጧቸውም ዋና ዋናዎቹን እስቲ እንያቸው:: ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት ማብራራያ የተነሳ ከተጻፉት ብሎጎች ልጀምር:: አቤ ቶክቻውን እናገኛለን: አቤ እንዲህ ይላል፤ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ስለመምህራኑ ማብራሪያ ተጠይቀው ማረሪያ ሰጡ!:: ሙሉውን ዜና ለማንበብ እዚህ ላይ ጠቅ ያድርጉ::
ኤፍሬም ኤሼቴ አደባባይ በሚሰኝው ብሎጉ “ጠ/ሚኒስትሩ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን በተናገሩት አልስማማም” የሚል ጽሁፍ አስነብቧል:: ከመጀመሪያው አንቀጽ፤
ማክሰኞ ሚያዚያ 9/2004 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ እንደተለመደው የምክር ቤቱ ክቡራን አባላት በንባብ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎቻቸው መልስ ሲሰጡ ተከታትያለኹ። ከጥያቄዎቹ አንዱ ወቅታዊው የሙስሊሞች ጉዳይ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው “መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አልገባም” የሚለውን በሰፊው ሲያብራሩ ቆዩ። አንዱ ማብራሪያቸው ስለ ሰላፊያዎች (አል-ሰላፊያ ወይም ወሐቢያዎች) ነው። ራሳቸውን “አል-ሰላፊዩን” የሚሉትና ትክክለኛውን የቁርዓን ትምህርት እንከተላለን የሚሉት የሙስሊም ክፍል የሆኑትና መሠረታቸውን በሳዑዲት አረቢያ ያደረጉት ጽንፈኛ ወገኖች በተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ “ወሐቢያዎች” ይባላሉ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ወሐቢያዎች እና ስለአክራሪነታቸው ማተት ስላልሆነ የዚህን ቡድን አስተምህሮ እና በኢትዮጵያ ላይ ስለ ጋረጠው ከፍ ያለ አደጋ “አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ” (ኤፍሬም እሸቴ፣ በ2000 ዓ.ም/ 2008 የታተመ) የሚለውን መጽሐፍ ማንበብ እንደሚቻል በመጠቆም አልፋለኹ።
ሙሉ ጽሁፉን ለማንበብ እዚህ ላይ ጠቅ ያድርጉ::
የሙስሊም ጉዳይ መጽሄት ሲኒየር ኤዲተር አክመል ነጋሽም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ንግግር በተመለከተ በፍትህ ጋዜጣ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዲስኩር ግዝፍት እና ግድፈት በሚል ጽሁፍ የራሱን አስተያየት ሰጥቷል:: ደረ ገጽ ላይ ላገኝው ባለመቻሌ እዚህ ላይ ትይይዙን ማኖር አልቻልኩም:: አርብ ሚያዚያ 12 2004 ከታተመችው ፍትህ ላይ ገጽ 12 ላይ ሊያገኟት ይችላሉ::
በዚህ ሳምንት ፌስቡክ እንደሌሎች ሀገሮች ሁሉ በኢትዮጵያም ለቁምነገር ሊውል እንደሚችል የታየበት አጋጣሚ አዲስ አበባ ላይ ታይቶ ነበር:: የአለም ደቻሳን ቤተሰቦች ለመርዳት እትዮጵያውያን በፌስቡክ ከያሉበት ተጠራርተው በዋቢሸበሌ ሆቴል የስነጽሁፍ ዝግጅት አድርገዋል:: የዚህ ስብስብ ስም ደጉ ኢትዮጵያዊ ይሰኛል:: በዚህም ሃያ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ከትኬት ሽያጭ እንደተገኝም በግሩፑ የፌስቡክ ገጽ ላይ ሪፖርት ተደርጓል :: ስለዚህ መልካም ተግባር ሪፖርተርም ከልብ ካለቀሱ እምባ እንደማይገድ ያስመሰከረ ስብስብ … በማለት በድረ ገጹ ዘግቧል:: በነገራችሁ ላይ የዚህ ግሩፕ ቁጥር አባላት 4000 በላይ ሆኗል እና አሁንም እያደገ ነው:: በተጨማሪም በዚህ መልካም ተግባር በርካታ ብሎግ ጻሃፊዎች እና የግሩፑ አባላት ደስታቸውን በግሩፑ የፌስቡክ ገጽ ገልጻዋል::
የኢትዮጵያ ብሎጎች እለት እለት እየጨመሩ ነው:: ነባር ጽሃፍትም የራሳቸውን ብሎግ እየጀመሩ ነው :: ዛሬ አንድ ሁለት ላስተዋውቃችሁ ። ከአደም ሁሴን ልጀምር አደም ሁሴን የአለም ደቻሳን ቤተሰቦች ለመርዳት በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ የስነጽሁፍ ዝግጅት ላይ ተግኝቶ የተሰማውን ስሜት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ገልጻል:: ግጥሙ የዝግጅቱ ለት የተገጠመ ባይሆንም ለዛ ያለው ግጥም እና መጣጥፍ በብሎጉ ላይ ብቻዩን አይደለሁም በሚል ርእስ አትሞ አሰነብቦናል :: እዚህ ጋር ጠቅ በማድረግ ተጋበዙልኝ ::
ሌላው ተስፋዬ አለማየሁ ነው:: እንደ አደም ሁሉ ተስፋዪም በሁለት የስነፅሁፍ ዘውጎች ፡ በግጥም እና በመጣጥፍ ብሎግ ከጀመረ አንድ አመት ሆኖታል:: በዚህ ሳምንት በበዕል አሳበው የዋጋ ቅናሽ አድርገናል እያሉ ገዢ ትርፍ የሚያጋብሱ ነጋዴዎችን የታዘበበትን ጽሁፉን “ቢግ ዲስካውንት. . . ወይስ ሜኪንግ ቢግ አካውንት ?” በሚል ርእስ አስነብቦናል:: እዚህ ጋር ጠቅ በማድረግ ዘና ይበሉበት::
ተስፋዬ ገ/አብ በዚህ ሳምንት ሁለት ጽሁፎች አስነብቦናል:: የጎጃም ልዕልት እና ጎሹም ሄደላችሁ የሚሉ:: የጎጃም ልዕልት ከምትለዋ አስቲ አንድ አንቀጽ እንካችሁ::
“የእናቷን ውበት ወርሳለች” ይሏታል። ርግጥ ነው፣ ወይዘሮ ላቀች ይህ ቀረሽ የማይባሉ ደርባባ ወይዘሮነበሩ። የቀድሞ የወጣትነት ወዘናቸው ወደ ልጃቸው ተሻግሮ ማየት ችለዋል። በዚህም ተባለ በዚያ ልጅቱየንጉስ ተክለሃይማኖት ሴት ልጅ ናት። ስምን መልአክ ያወጣዋልና ስሟ ንግስት ይባላል። ስለዚህ ቆንጆ ናት።ከቁንጅናዋ በላይ ግን ሊጠቀስላት የሚችል ቁምነገር ነበራት። ከደብረ ኤልያስ ገዳም በመጡ ሊቃውንትፅህፈትና ቅኔ ተምራ ነበር። አባቷ እያሉ አጊጣለች። ርግጥ አሁን ፀሃይ ጠልቃባት ነበር…
ሙሉውን ጽሁፍ ትይይዙን ጠቅ በማድረግ ዘና ያንብቡት::
አሁን ሱስ ወደሲያዘኝ የፍሰሀ ተገኝ ብሎግ ልውሰዳችሁ:: ፍሰሀ ዛሬ ደግሞ የሀገራችንን የእግር ኳስ መሰረታዊ ችግር ገራ ገር በሆነ ቋንቋ አሰነብቧል:: ደግሜ ደግሜ ደግሜ አነበብኩት እጅግ የሚመስጥ ገለጻ ነው:: እስቲ ትንሽ ቀንጨብ አድርጌ ማጓጓያ ላቅርብ:
በቅርቡ በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የኢትዮጵያዎቹ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰሜን አፍሪካዎቹ ተጋጣሚዎቻቸው ጋር ከሜዳቸው ውጪ ያደረጓቸው ጨዋታዎችን ካየሁ በኋላ በፍጥነት አእምሮዬ ላይ የመጣብኝ ነገር ቢኖር “የኢትዮጵያ እግርኳስ ተጨዋቾች የሚያንሳቸው ነገር ቁመት፣ ጉልበትና የኳስ ችሎታ ሳይሆን ያላቸውን ነገር እንዴት መጠቀም እንዳለባቸውና ኳስ ተጋጣሚያቸው እግር ውስጥ ስትገባ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አለማወቃቸው ነው” የሚለው ነበር።
ብዙውን ጊዜ በክለብና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የኢትዮጵያ ቡድኖች ከውጪ ቡድኖች ጋር ከተጫወቱ በኋላ የተጋጣሚ ቡድኖቹ አሰልጣኞች ስለኢትዮጵያ ቡድኖች የሚሰጡት አስተያየት ተመሳሳይ ነው፤ “ጥሩ የኳስ ችሎታ አላችሁ” በሚል ይጀምርና “ግን…” ብሎ በሚቀጥል አረፍተ-ነገር የሚጠናቀቅ። “ግን…” ብሎ የሚቀጥለው አስተያየት ቀሪዎቹን አንድ ቡድን ሊኖረው የሚገቡትን ብቃቶች የሚያጠቃልሉ ናቸው።
እንደኔ የእግር ኳስ ፍቅር ካሎት ቀሪውን ትይይዙን ጠቅ በማድረግ ግንዛቤዎን ያዳብሩበት::ዛሬ የምወደው ባርሴሎና ከማልወደው ሪያል ማድሪድ ይጫወታል ድል ለባርሳ እያልኩ የፍሰሀን ምልከታ በተግባር ለማስተዋል ይመቻል እና ተደሰቱበት::
እንዳልክ አንተ በግሎባል ቮይስ የጻፍከውን ረስተኽው ነው?ወይስ ለማካተት አልፈለክም? ስለወደድኩትና ስለለፋኽበት ቢነበብ ደስ ይላኛል::
ለዛሬው እንደሁሌው ምስጋና !!
ማንበብ ለሚሻ
http://globalvoicesonline.org/2012/04/16/ethiopia-teddy-afros-new-album-stirs-up-online-discussion/