የኢትዮጵያ ብሎጎች ምን ጻፉ?

የሀገራችን መገናኛ ብዙሀን አውቀው በፍርሀት ሳያውቁ በስህተት ጆሮ ዳባ ያሏቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች ለማንበብ ፡ ለመስማት አማራጩ ፌስቡክ ትዊተር እና የተለያዮ ብሎጎች እየሆኑ መምጣታቸውን ለማወቅ አዲስ አበባ በየጥጋ ጥጉ ያሉ የኢንተርኔት ካፌዎችን ለደቂቃ መጎብኝት በቂ ነው:: በሳምንቱ ማን ምን ከተበ? ምን አስደመመው? ምን ተነተነ?ምን አሳዘነው? ምን አስደሰተው? የሚለውን በአጤሬራ መልክ ማቀመስ ደግሞ ባይጠቅምም አይጎዳም ስለዚህ ባሳለፍነው ሰሞነ ህማማት ኢትዮጲያውያን የፌስቡክ የትዊተር እና የተለያዮ ብሎግ ተጠቃሚዎች ምን አሉ? በምን ተደሰቱ ? በምን አዘኑ? በምንስ ተማረሩ? እንደተለመደው ከብሎግ ክለሳ እጀምራሁ:: ተከተሉኝ፦

ከእንጨት መርጦ ለታቦት ከብሎግ መርጦ ለትኩረት ልበልና እስቲ ቀልቤን የሳቡኝን ላካፍላችሁ:: በዚህ ሳምንት የተስፋዬ ገብረአብ ብሎግ የቅዳሜ ማስታወሻ በመጋቢት ወር ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን አስመልክቶ ምሁራን በተለይ በውጪ ያሉ ከተለያዮ አንግሎች አንጻር የሰጡትን አሰተያየትና የሀገሪቱን እጣ ፈንታ የራሱን ምልከታ ጨምሮ አስነብቦናል:: የጽሁፉ የመጨረሻው መስመር ገለልተኛ ስለመሰለኝ እዚህ ልጥቀስላችሁ እንዲህ ይላል ፦

የቆየውንና ጊዜው ያለፈበትን በጥላቻና በጀብደኝነት ላይ ተመስርቶ የነበረውን አንድነት በመተው፣ ሰብአዊነትንና እኩልነትን ባረጋገጠ መልኩ ኢትዮጵያዊነትን መገንባት ይገባል!

መቼም ገለልተኛ ምናምን ያልኩበትን መንፈስ ትረዱልኛላችሁ:: ቀሪውን እናንተው እዚህች ላይ ጠቅ ያአድርጉ እንዲህም ይባላል ለካ ታስብሎታለች:: የቅዳሜ ማስታወሻ ለግዜው ኢትዮጵያ ውስጥ አልታሸገም::

ቀጠልኩ ወደ አቤ ቶክቻው:: ከዚህ ሳምንት የአቤ ጽሁፎች ቀልቤን የሳበችው የፀሎተ ሀሙስ እለት ያተማት የትላንት በያይነቱ የምትለዋ ጽሁፉ ናት:: ፌስቡክ ላይ ሞቅ በለው የሰነበቱ ወሬዎችን በአጤሬራ መልክ በሀዘን በደስታ እንደገና በሀዘን ካዛ ደግሞ በሽሙጥ ከራሱ ስሜት ጋር አዋዝቶ አቅርቧል:: ትንሽ ልጥቀስ፦

“እምዬ ኢትዮጵያ የጀግኖች እናት እስቲ ፈልጊልኝ የሚከራይ ቤት” የሚል ፅሁፍ ተለጥፎ አየሁ። ይህንን ፅሁፍ ከዚህ በፊትም አይቼዋለሁ። እውነትም የሚከራይ ቤት እንኳ ኢትዮጵያችን ብታገኝልን ቢያንስ በየ አረብ ሀገራቱ እህቶቻችን አየሰቃዩም ነበር። ብዬ እያሰብኩ… ወረድ አልኩ። አሁን አሪፍ ዜና አየሁ። እስክንድር ነጋ ታላቅ አለም አቀፋዊ ሽልማት አገኘ!
ታዋቂው እና ተወዳጁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ፔን ኢንተርናሽናል” ከተባለ ድርጅት PEN/Barbara Goldsmith Freedom to Write Award. የተባለውን ሽልማት አገኝቷል።

እስክንድር ነጋ የ PENንን ሽልማት ማግኘቱ በዚህ ሳምንት እጅግ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን አስፈንድቋል:: ዜናው እንደተሰማ ዜናውን ያበሰሩትን ደረገጾች ትይይዝ በየፌስቡክ ገጾቻቸው ለጣጥፈዋቸው ነበር:: ብዙዎቹም ዜናውን መውደዳቸውን likeን ጠቅ በማድረግ ገለጸዋል:: መቼም እንዲህ አይነቱን ዜና አዲስ ዘመን ላይ ማንበብ እንዴት እንደምናፍቅ:: ለማናቸውም እኔም ደስ ብሎኛል:: ይገባዋልም::

ከወርሃ የካቲት ጀምሮ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ትኩርት ስቦ የነበረው በዋልድባ ገዳም ዙሪያ የተነሳው ውዝግብ ነው:: በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 1 ፤ 2004 ዓ.ም አንድ አንድ አድርገን የሚባል ብሎግ አስገራሚ ሊባል የሚችል ዜና አስነብቦናል:: ከመጀመሪያው አንቀጽ፦

አባቶች በጸሎት እየበረቱ ይገኛሉ ፤ አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት በቦታው ላይ ያለው ስራውን የሚያከናውን ተቀጣሪመሃንዲስ ባልታወቀ ምክንያት ሞቷል ፣ ስው ለመስራት የተቀመጡ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎቹ በየሰአቱእየተበላሹይገኛሉ ፣ ካልታወቀ ቦታ የተለያዩ አውሬዎች እየወጡ ሰራተኛን መተናኮል ጀምረዋል::

ከስፖርት ብሎጎች የፍሰሀ ብሎግ ዛሬ ደግሞ ስለተወዳጇዋ ደራርቱ “ሳቂታዋ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግስት” በሚል ርእስ በጣፋጭ ቋንቋ ያወገናል:: በአዲስ አበባ FM ራዲዮኖች በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እንጨት እንጨት ያለ ዘገባ ለተሰላቸ ምነኛ ምርጥ አማራጭ ነው:: የሀገራችንን የአትሌቲክስ ጀግኖች ያልተነገሩ ታሪኮች እንዲህ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ፈልፍሎ የሚያቀርብልን አጠተን ተሰቃየን የሚሉ ጓደኞቼ በርካቶች ናቸው:: ከመጀመሪው አንቀጽ፦

ኦሎምፒክ ምን እንደሆነ ከማወቄ በፊት የእሷን ስምና ድሏን ነበር የማውቀው። ስሟ በሬዲዮ በተደጋጋሚ ሲጠራ ስለሰማሁት አእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ተቀምጧል። “የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነች” የሚለው ጩኸት ልቤን አልሰረቀውም፤ ልጅ ነበርኩና የኦሎምፒክን ዋጋና ምንነት ባለማወቄ። “ሮጣ ተፎካካሪዎቿን እንደ ጭራ ከኋላ አስከትላ አሸነፈች” የሚለው ድምጽን ለማስተናገድ ግን አልተቸገርኩም። ምክንያቱም እየተሯሯጠና አቧራ እያቦነነ ለነበረ ልጅ ሩጫ፣ መቅደምና መቀደም ምን እንደሆኑ ለይቶ ለማወቅ አያስቸግረውምና።

ቀሪውን እዚህ ላይ ጠቅ አድርገው ያንብቡ:: በመጨረሻም ከራሴ ብሎግ ስለልማታዊ ጋዜጠኝነት የጻፍኩትን እንካችሁ:: መልካም ፋሲካ::

One thought on “የኢትዮጵያ ብሎጎች ምን ጻፉ?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.